This blog post is in Amharic, if you are seeing boxes download fonts here.
ሰሃራ በታች ከሚገኙ አገሮች በተለይም ኢትዮጵያና ጎረቤት ኬንያ ስለ ቁም እንስሳት ሀብታቸው ብዙ ይባልላቸዋል፡፡ ይሁንና ተደጋግሞ እንደሚገለጸው አገሮቹ ካላቸው እምቅ አቅም አንፃር ተጠቃሚነታቸው ሲፈተሽ ከባህር ላይ በጭልፋ የመጥለቅ ያህል የሚጋነን ነው፡፡
ሌላው ቀርቶ «…ከከብቶቹ በፊት ነው የሞተው እርሱ!» የሚለውን አገርኛ ብሂል ነጥለን ስናይ፤ እንስሳት በኢትዮጵያ ከአርቢዎቻቸው ጋር ያላቸው ቅርበት የቤተሰብ አባላት ያህል ጥልቅ መሆኑን ለመረዳት ያስችለናል፡፡ ይሁንና በአርቢዎቻቸው ይሄን ያህል ትኩረት የሚያገኙት የቁም እንስሳት እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ አገር የሚያስገኙት ጥቅም «ባለህበት እርገጥ» የሚባል አይነት ነው፡፡
ይሄን በአግባቡ የተረዳው መንግሥት ዘርፉ ላይ የሚታዩትን እንቅፋቶች በማስወገድ ተገቢውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማስገኘት በርካታ ውጥኖችን ነድፎ ለከርሞ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ሰሞኑን የምስረታውን 40ኛ ዓመት በማክበር ላይ የሚገኘው ዓለም አቀፉ የቁም እንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት (ILRI) ዘርፉን ይበልጥ ለማጎልበት ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ እንደሚሠራ ጠቁሟል፡፡
በክብረ በዓሉ መክፈቻ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን «በበርካታ የልማት ማነቆዎች ምክንያት ኢትዮጵያ ከቁም እንስሳት ሀብት ማግኘት ያለባትን ጥቅም አላገኘችም» በማለት ዘርፉ በቀጣይ ቁልፍ የመንግሥት የትኩረት ማረፊያ እንደሚሆን ያነሳሉ፡፡
በቅርብ ዓመታት ውስጥ የዓለማችን ህዝብ ቁጥር ከሰባት ቢሊዮን በላይ መድረሱ ይታወሳል፡፡ የዜጎች ቁጥር በዚህ እድገት ከቀጠለ እ.አ.አ በ2050 ዓለም ከዘጠኝ እስከ አስር ቢሊዮን ልጆች ይኖሯታል ተብሎ ይገመታል፡፡ በመሆኑም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሉት ይሄ የሰዎች ቁጥር ፈጣን እድገት አሁን ያለውን የዓለማችን የምግብ ምርት እስከ 70 በመቶ ማሳደግ እንደሚገባ የሚያስገድድ ይሆናል፡፡ ለእዚህ ደግሞ ሰፊ የግብርና ምርት ውጤት ባለቤቷ አፍሪካ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ በነቃ መልኩ ተጠቃሚነቷን ማስጠበቅ ይቻላታል፡፡ ምክንያቱም የዓለማችን ሰፊ የምግብ ግብዓት በመሆን የሚታወቀው የእንስሳት ተዋፅኦ በአፍሪካ በመኖሩ ነው፡፡
የተጠቃሚነት እድሉን መፃዒነት ወደ ኢትዮጵያ አምጥተን ስንመለከትም ሁኔታው ተቀራራቢ ነው፡፡ ሀብቱ የሌሎች አህጉራትን ምግብ ፍላጎት ከመሙላቱ በተጓዳኝ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለምጣኔ ሀብት እድገት፣ ድህነት ቅነሳ እና የምግብ ዋስትና በዘላቂነት መረጋገጥ ቀጥተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ «የቁም እንስሳት ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ አይነተኛ ሚና ይጫወታሉ» የሚሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዘርፉን ማሳደግ በተለይም ከእንስሳት ተዋፅኦ የሚገኙ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ፕሮቲንና ካሎሪስ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት እንደሚያስችል ይናገራሉ፡፡ ከእንስሳት ተዋፅኦ 26በመቶ ፕሮቲን እንዲሁም 13 በመቶ ካሎሪስ እንደሚገኝም እንዲሁ፡፡
በቀጣይ ዓለማችን ላይ ከሚጠበቀው የነዋሪዎች መብዛት በተጨማሪ ቀጥተኛ የእንስሳት ውጤቶች ፍላጎት ማደጉ የማይቀር ነው፡፡ ለአብነትም ሌላውን ዓለም ትተን ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገሮች ብቻ ብንመለከት የወተት ፍጆታ በጥቂት አሰርት ዓመታት ውስጥ አሁን ካለው ሦስት እጥፍ እንደሚያድግ ይተነበያል፡፡ በመሆኑም ባለሙያዎች እንደሚሉት እንስሳትን ከተለያዩ በሽታዎች በመጠበቅ ዘርፉን ቁልፍ የኢኮኖሚ መሰረት ማድረግ ይቻላል፡፡
አቶ ደመቀ እንደሚሉት ታዲያ በተለይም የአነስተኛ አርሶ አደሮች ምርታማነት ሥርዓት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት በማደግ ላይ ለሚገኙ አገራት ወሳኝ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደ «ኢልሪ» ያሉ ምርምር አድራጊዎች በአነስተኛ አርሶ አደሮች ላይ ማተኮራቸው ዘላቂነት ላለው የግብርና ልማት መሰረት ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ ተጠቃሚነት አሁንም ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ባለፉት ዓመታት እንደታየው አገሪቱ ከቁም እንስሳት እና ስጋ ሽያጭ ቀጥተኛ የወጪ ንግድ ገቢዋ 262 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብቻ ነው፡፡ ጉዳዩን ይበልጥ አንገብጋቢ የሚያደርገው ደግሞ ዘርፉ ሊሰጥ የሚችለው ጥቅም ከተጠቀሰው ገቢ በአራት እጥፍ ማስገኘት የሚችል መሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም እንደ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ በመሰረተ ልማት፣ በቀልጣፋ የገበያ ሥርዓት፣ በእንስሳት ጤና እና በእንስሳት ጊዜያዊ ማቆያ ላይ የሚታዩ ችግሮች መፈታት አለባቸው፡፡
ለእዚህ ደግሞ ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ ጊዜ ወሳኝ ሆኗል፡፡ በተባለው ወቅት በዘርፉ እሴት በመጨመር ለድህነት ቅነሳ ተግባር አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል፡፡ 40ኛ ዓመቱን የሚያከብረው «ኢልሪ» በአቅም ግንባታ እና ፕሮግራም ማስተባበር ዙሪያ ያደረገው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ በተለይም ለቀጣዮቹ አስር ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ የቁም እንስሳት ልማት መሪ ዕቅድ በተያዘው ዓመት እንደሚተገበር አቶ ደመቀ አስታውቀዋል፡፡ መሪ ዕቅዱም በዋናነት ብሔራዊ የቁም እንስሳት ልማትን ወደተሻለ ደረጃ ማሳደግ የሚያስችል መመሪያዎችን ያቀፈ ነው፡፡ ተግባራዊነቱም ከተያዘው ዓመት ጀምሮ ይሆናል፡፡
ኢትዮጵያ ከእንስሳት ሀብቷ የምትጠቀምበት ጊዜ የተቃረበ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ከአጠቃላዩ የግብርና ንዑሱ ዘርፍ በዚህ ላይ ትልቅ ድርሻ አለውና፡፡ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ተፈራ ደርበው የሚሉትም ይሄንኑ ነው፡፡ «ከግብርና ውጤት ገሚሱን የሚሸፍነው የቁም እንስሳት ንዑስ ዘርፍ ያሉበትን ማነቆዎች በመቅረፍ በቀጣይ እንደሚያድግ የሚጠበቀውን የአገር ውስጥ የወተት እና ሥጋ ፍላጎት ለማሟላት አቅሙን ማጎልበት ይገባል» ይላሉ፡፡ ከአጠቃላይ የአገሪቱ ውጭ ምንዛሪ ገቢ ከ16 እስከ 19 በመቶ ከእንስሳት ሽያጭ የሚገኝ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ ለተገቢው እድገት እንቅፋት የሆኑ ተግዳሮቶች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡
ፈጣን የዜጎች ቁጥር መጨመር፣ የከተሞች መስፋፋት እንዲሁም የአገር ውስጥ የስጋ፣ የወተትና እንቁላል ፍላጎት ማደግ ከተፅዕኖዎቹ መካከል እንደሚጠቀስ አንስተዋል፡፡ አቶ ተፈራ እንደሚሉት እነዚህ ሁሉ ችግሮች ተዳምረው በሁለት እጥፍ ሊያድግ የሚችለውን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ባለበት እንዲቀር አድርጎታል፡፡ በተጨማሪም አገሪቱ የምትገኝበት ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ የቁም እንስሳትን ለጥቂት የገልፍ እና አፍሪካ አገሮች ገበያ ብቻ ተደራሽ እንዲሆን አስገድዷል፡፡
በመሆኑም መንግሥት በቀጣይ ዕቅድ ትኩረት ሰጥቶ የሚንቀሳቀሰው የእንስሳት ሀብት ልማትን የግብርናው መሪ ለማድረግ መሥራት ላይ ነው፡፡ ለእዚህም በ«ኢልሪ» የተቀረፀው የቁም እንስሳት መሪ ዕቅድን መተግበር ወሳኝ ነው፡፡ ከአገር አቀፍ እንቅስቃሴው በተጨማሪ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራም (ካዳፕ) በኩል ዘርፉን ለማሳደግ እየሠራች ነው ብለዋል፡፡
እ.አ.አ ከ1974 ጀምሮ ሥራውን የጀመረው ኢልሪ ባለፉት ዓመታት በእንስሳት አመጋገብ እና ጤና አጠባበቅ፣ በአርብቶ አደሩ፣ በእሴት ሰንሰለት፣ በመሬት አጠቃቀምና ሌሎች ቁልፍ ተግባራት ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶች ሲያከናውን መቆየቱንም ጠቅሰዋል፡፡ ከእንስሳት ምርምር በተጨማሪ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ ኢልሪ የራሱን አስተዋፅኦ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ኢትዮጵያ እየተገበረች የምትገኘው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ለእዚህ ተጠቃሽ ነው፡፡ በተጨማሪም የካርበን ልቀትን ለመቀነስና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ላይ በየክልሉ በርካታ ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡ እስካሁን በተሠሩት ብቻ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረውን በረሃማነት በመቀነስ የደን ሽፋኑን ከሦስት በመቶ ወደ 11 በመቶ ማሳደግ መቻሉን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
የግብርና ሚኒስትሩ እንደሚሉት ታዲያ በተካሄዱ ምርምሮች ከኢልሪ የዘር ባንክ በሺዎች የሚቆጠሩ የዘር ምርምሮች እውቅና ሊያገኙ ችለዋል፡፡ ለደን ከሚሰጡት ግብዓት በተጨማሪ ለእንስሳት መኖ ተመራጭ የሆኑ ዝርያዎች ተገኝተዋል፡፡ የአገሪቱ የቁም እንስሳት ኤክስፖርቱ በሕገወጥ ግብይት እየተፈተነ ይገኛል፡፡ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ወንድይራድ ማንደፍሮ ይሄ እውነት መሆኑን ጠቅሰው፤ ችግሩን ለመቅረፍ በርካታ ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡ የእንስሳት ጤና፣ አገልግሎት አሰጣጥ፣ የትራንስፖርት ሎጂስቲክስ ችግር እንዲሁም የጊዜያዊ ማቆያዎች አለመሟላት መሰረታዊ ማነቆዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም ይሄን በመቅረፍ ገቢን ለማሳደግ ይሠራል ብለዋል፡፡
በጎረቤት አገራት ሚዛናዊ የሆነ የእንስሳት አቅርቦት አለመኖርም ሌላው ችግር ተብሏል፡፡ ሕገወጥ ግብይቱም የሕግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀለት ይገኛል፡፡ የግብርና ልማት ዓለም አቀፍ ድጋፍ ፕሬዚዳንት ካናዮ ንዋንዜ እንደሚሉት በቀጣዮቹ ሁለት አሰርት ዓመታት የዓለም የምግብ ፍላጎት በእጥፍ እንደሚያድግ ይጠበቃል፡፡ በመሆኑም የቁም እንስሳት ሀብት ያላቸው አገራት ኢንዱስትሪው የሚፈጥርላቸውን መልካም እድል መጠቀም ይገባቸዋል፡፡
ከእነዚህ መካከል ደግሞ አንዷ ኢትዮጵያ በመሆኗ ትኩረት ልትሰጠው ግድ ነው፡፡ ኢልሪ በበርካታ ጉዳዮች ዙሪያ ለሁለት ቀን የሚወያዩ ባለሙያዎች ጋብዟል፡፡ ባለፉት አራት አሰርት ዓመታትም በተለያዩ አፍሪካ አገራት በፖሊሲ፣ በገበያ፣ በቁም እንስሳት እና ዓሣ፣ በምግብ ዋስትና እና በአየር ንብረት ለውጥና ተያያዥ ዘርፎች ምርምር ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ሌላ የዜና ጥንቅሮች:
- አለምአቀፍ የእንሰሳት ምርምር ኢንስቲትዩት 40ኛ አመቱን በማክበር ላይ ነው
- Livestock production crucial to improve smallholder farmers livelihood
- New livestock master plan for Ethiopia to help secure more revenue from sector
- ኢልሪ (ILRI) 40ኛ ዓመቱን እያከበረ ነው: የቁም እንስሳት ዘርፍን ኢኮኖሚያዊ ድርሻ ለማሳደግ እየተሠራ ነው
- መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች መጨመርን ተከትሎ የሚያድገውን የምግብ ፍላጎት ለማሟላት የቁም እንስሳት ምርታማነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል